All Reviews
Book cover
ብቻዬን ቆሚያለሁ

by አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ

5.0 avg · 1 review
T
Tsegaw Mamo
4 reviews · 0 followers · September 28, 2026
5/5

ብቻዬን ቆሜያለሁ I Stand Alone

"ለነጻነት ያለን ተስፋ በሞታችን ይሳካል"... የእኔ እውነታ(reality) ሞት ነው" እንዲሉ" በአልቦ ዘመድ" መጽሐፋቸው ፤ ከፍተኛ ሹመትን፣ ዝናንና ሀብትን ንቀው ለጭቁን ኢትዮጵያውያን ነጻነት በዚህች ምድር ላይ ድህነትንና ባይተዋርነትን ከመረጡት ጥቂት ኢትዮጵያዊ ሰው አንዱ ብርሃኑ ድንቄ ናቸው ። እርሳቸውም እንዲህ አሉ "የአሜሪካ አምባሳደር ነበርኩ አሁን ግን ባይተዋር ነኝ" እግራቸው የእውነትን መንገድ ሊረግጥ ሲያቀና መላው ዓለም ሸሻቸው።የአሜሪካ ነጻ ፕሬሶች ሁሉ ሳይቀሩ የእርሳቸው ቃለ መጠይቅና ንግግር እንዳይተላለፍ አገዱ! ከጎናቸው የነበሩ ታላላቅ የዓለም ዲፕሎማት ሁሉ ሸሿቸው፤ እርሳቸው ግን በስደት አገር በቅኔያቸው እቅፍ ውስጥ ብቻ ተሸሸጉ ፣ የእውነት አርነት የምታወጣቸውን የሞትን ጽዋ ከነ ክብራቸው ሊጎነጯት ናፈቋት! ለእርሳቸው እውነት ማለት ሞት ነውና! አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ በእንጦጦ ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት የተማረ ሊቅ ነበር። አጼ ኃይለሥላሴ በልጁ የሰላ ቅኔያዊ ትችት ተማርከው ለታላላቅ ሹመት አብቅተውታል።በተሾመበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ ለአገርና ለእውነት በመቆም በሠራው ሥራ ንጉሡን አስደምሞአቸዋል ። በተሾመበት የመንግሥት ተቋም ሁሉ የነቀዙ የሙስና አሰራሮችን ለብቻው ታግሎአቸዋል! አንድ ጊዜ የፖስታ ፣የቴሌፎንና የቴሌግራፍ ምክትል ሚኒስቴር ሆኖ በተሾመበት ሰዓት ንጉሣውያን ቤተሰቦችና የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያልተከፈለ ውዝፍ እዳ በአስቸኳይ እንዲከፍሉ ካስጠነቀቀ በኋላ ባለመክፈላቸው የሁሉንም የሥልክ አገልግሎት አቋርጦታል።ልዑል አልጋወራሽ አስፋወሰን ኃ/ሥላሴ፣ልዑል ሳህለ ሥላሴ ፣ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ፣ራስ አበበ አረጋይ ፣መኮንን ሀብተወልድ እና ሌሎችም እየጠሩ ይሰድቡትና በንጉሡ ፊት ይከሱት ነበር። በዚህ ሁሉ ሂደት እርሱ ብቻውን ይታገል ነበር። አምባሳደር በርሃኑ ድንቄ በሳውዳረቢያ፣ በጂቡቲና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ የሰራ ነው። ንጉሡ የመንግሥት ሥርዓታቸውን ያሻሽሉ ዘንድ በተደጋጋሚ የወተወተ ቢሆንም ባለመስተካከሉ በመጨረሻ በአሜሪካን ሀገር ኃላፊነቱን በራሱ ፈቃድ ሊለቅ ችሏል። አምባሳደር ብርሃኑ " እኔን በብርቱ የሚያሳስበኝ የአገራችን መጭው ዕድል ብቻ ነው" ይላል። ለንጉሡ ከ10 ጊዜ በላይ ደብዳቤ የጻፈላቸው ሲሆን በአንዱ ደብዳቤ ላይ እንዲህ ይላል "ከሁሉ በላይ ግርማዊነትዎ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለው እንቅስቃሴ በተለይ የብሔረሰቦች ጥያቄ በአንድ ወቅት ፈንድቶ አደጋ እንደሚያመጣ እንደሚገነዘቡት እገምታለሁ" በማለት ትንቢት ተናግሮ ነበር። አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ የደርግ መንግሥትም ሥርዓቱን ያሻሽል ዘንድ የተግሳጽ ደብዳቤ ጽፈውለት ነበር ። ከደብዳቤው ውስጥ እንዲህ የሚል ነበረበት። "አሁን ግን ንጉሠ ነገሥቱ ምን ይቆጠሩ ተብሎ ነው ስማቸውን የምታጠፋት ? ወደ ፊት የእናንተስ ምን እንደሚመስል ታውቃላችሁ? " "10ኛውን ዓመት ስታከብሩ የሚሰማችሁ ምንድነው ? የሥራ ጓደኞቻችሁንና አለቆቻችሁን ያለ አንዳች ፍርድ ደብድባችሁ መግደላችሁ ነውን? ኢትዮጵያ የችጋር፣ የበሽታ፣ የፍርሃት፣ የጭንቀት፣የዋይታ፣ የግፍ አገር መሆኗ ነውን? እነ ቴዎድሮስን የመሳሰሉ ጀግኖች እንዳልተፈጠሩባት ያህል ኢትዮጵያ ባንድ ትንሽ አገር በኩባ ወታደሮች መጠበቋ ነውን?" በማለት ቁጭታቸውን ጽፈውላቸው ነበር። አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ከ10 በላይ መጽሐፍትን ጽፈው " አድሎአዊነትን አጥብቄ ስምጠላ በስደት መሞትን እመርጣለሁ" የሚለውን የጳጳስ ግሪጎሪ 7ኛን ጥቅስ እየጠቀሱ ብቻቸውን ከእውነት ጋር ኖረው ብቻቸውን አርፈዋል። በግለሰብ ደረጃ ለሀገርና ለትውልድ መሥዋዕትነት በመክፈል አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄን ማን ይወዳደራቸው ይሆን ? ምስጋና ይኸንን መጽሐፍ ለተረጎመልን ለተስፉ ረፌራ ጫላ ይሁን!
Comments (0)
Login to leave a comment.
T
Tsegaw Mamo
4 reviews · 0 followers
View All Reviews
Have you read this book?

Share your own review and help the community.

Write a Review
Get it on Google Play