All Reviews
Book cover
የብርሃን ጥሞና

by ሳባ ሲሳይ

5.0 avg · 1 review
ሐዋዝ የሻነህ
1 reviews · 2 followers · May 14, 2026
5/5

የብርሃን ጥሞና

የመጽሐፍ ርእስ :- የብርሃን ጥሞና ገጣሚ:- ሳባ ሲሳይ ዘውግ :- የግጥም ስብስብ የገጽ ብዛት:- ፻፲፪ የታተመበት ዓ.ም:- ፳፻፲፰ ማቲው አርኖልድ የተባለ ገጣሚና የሥነ ጽሑፍ ባለሙያ "ሥነ ግጥም በእውነት እና ውበት ላይ የተመሰረተ የሕይወት ሂስ ነው።" ይላል። ከዚህ ሐሳብ በመነሳት ግጥምን መሄስ ማለት ሕይወትን በመታዘብ የተሰጠን ሂስ መሄስ እንደማለት ነው። "የሳባ ግጥሞች ምን ይመስላሉ?" ስንልም ሳባ የሰውን ልጅ ሕይወትና አኗኗር በምን አይነት ትዝብት ሂሳዋለች የሚለውን ጥያቄ የመመለስ ጉዳይ ነው። የሕይወት ሂስ ሲባል:- የሰውን ልጅ:- ✍️ሥነ ምግባር ✍️አመለካከት ✍️የሕይወት ፍልስፍና ✍️እምነትንና የመሳሰሉትን የሚያጠቃልል ሲኾን እኒህን የመኖር ጣጣዎች ውበት እና ለዛ ባለው መንገድ የማቅረብ ስልት ነው። ከዚህ ሐሳብ በመነሳት ሳባ ሲሳይ በግጥሞቿ ውስጥ የሰውን ልጅ ሕይወት እና የመኖር ጣጣዎች በምን ያህል ርቀትና ምጥቀት ለመዳሰስ ሞክራለች የሚለውን እናያለን። እስኪ በመጀመሪያ ገጣሚት ሳባ ሲሳይ ለግጥሞቿ ስብስብ መጠሪያነት ርእስ አድርጋ የመረጠችውን "የብርሃን ጥሞና" የተሰኘ ሐረግ ከማመሥጠር እንጀምር። ✍️የብርሃን ጥሞና ብርሃን እና ጥሞና ሲገናኙ የሰው ልጅን ውስጣዊ ሰላም እና ንቃተ-ህሊና የሚገነቡ ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ሆነው እናገኛቸዋለን። ​እስቲ የሁለቱን ተናነጠላዊ እና ተጣምሯዊ ምሥጢር እንመልከት። ​፩. ብርሃን ​ብርሃን በመንፈሳዊውም ሆነ በአእምሮአዊው ዓለም የዕውቀት፣ የተስፋ እና የመገለጥ ምልክት ነው። ብርሃን ​መንገድ አመላካች ነው፦ በጨለማና ግራ መጋባት ውስጥ ላሉ ሁሉ አቅጣጫን ይጠቁማል። ​፪. ጥሞና ​ጥሞና የልብ እና የአእምሮ ዝምታ ነው። ከውጫዊው ዓለም ረብሻ እና ጫጫታ ወጥቶ ወደ ውስጥ የመመልከት ጥበብ ነው። ​ሰው በዝምታና በጥሞና ውስጥ ሲሆን ብቻ ነው የራሱን ድምጽ መስማት የሚችለው። ​ጥሞና ግርድፍ ስሜቶችን እና የተወዣበሩ ሐሳቦችን አጣርቶ ሰላምን የመፍጠሪያ መንገድ ነው። ​✍️የብርሃን እና የጥሞና ተጻምሮ ምሥጢር ​"የብርሃን ጥሞና" ስንል በዝምታ ውስጥ የሚገኝ የአዕምሮ ብርሃንን ወይም አማናዊ ነጻነትን ማሰብ ነው። ይህ ውህደት ብዙ ጥቅሞችን የሚሰጥ ሲኾን ከእነዚህም መካከል:- ​ውስጣዊ መገለጥ፦ አእምሮ በጥሞና ሲረጋጋ አዳዲስ እና ብሩሃን ሐሳቦች መፍለቅ ይጀምራሉ። ​ከጭንቀት መውጣት፦ በዙሪያችን ያሉ ጨለማዎች የሚገፈፉት በጥሞና በምናገኘው ውስጣዊ ብርሃን ነው። ​ውሳኔ የመስጠት ብቃት፦ አንድ ሰው በጥሞና ውስጥ ሆኖ ነገሮችን ሲመለከት፣ ብሩህ የሆነ ውሳኔ ላይ መድረስ ይችላል። ​"ብርሃን ወደ ውጭ እንድንመለከት ይረዳናል፤ ጥሞና ደግሞ ወደ ውስጥ እንድንመለከት ያደርገናል። ሁለቱ ሲገናኙ ግን ሙሉ ሰው እንሆናለን።" ​ እንግዲህ ገጣሚት ሳባ ሲሳይ ለግጥም ስብስብ ሥራዎቿ መጠሪያነት የመረጠችው "የብርሃን ጥሞና" የተሰኘው ሐረግ ከጥበብ አስተውሎት የተቃባ ፤ ከአመሥጥሮ ያልተዛባ ልክክ ያለ ምችቹ ርእስ ነው ብለን መመሥከር እንችላለን ማለት ነው። የሳባ ግጥሞች ብዙ ሐተታ እያስነሱ የሚያስወሩ ቢኾኑም ለአብነት የሚኾኑንን ጥቂት ስንኞች እያነሳን ለማየት እንሞክር። ✍️ከመጽሐፉ መግቢያ በፊት ከተቀመጠው ከፍ ያለ ግጥም ብንጀምር ገጣሚት ሳባ "ከእጦት የተገኘ ማንነት" በሚል ግጥሟ ውስጥ እንዲህ ስትል እናገኛታለን። የሳባ ስንኞች ቅምሻ (1) " ልፍስፍስ ናት ብላ ዓለም እንዳትገፋኝ፣ አከሰርሽኝ ብሎ እግዜር እንዳይተፋኝ፣ ሰብረሽኝ ስትሄጂ መጠገንን ዐወቅሁ፣ ወደ እንባ ባሕር በገፈተርሽኝ ልክ በሳቅ ጎዳና ፊት ልመና ተሰለፍሁ። ...ልጄ ሆይ... ጥቁር እና ነጩን እያደበላለቅሽ በሰጠሽኝ ቀለም ታሪኬ ተጻፈ፣ በውልደትሽ ስቄ በሞትሽ ማልቀሴ ሰው አርጎኝ አለፈ" --------------------------------- ✍️ሳባ በዚህ ግጥም ውስጥ የሰውን ልጅ ማንነት የሚፈትሽ እጅግ ጥልቅ የሆነ የህላዌ ፍልስፍናን አስቀምጣለች።  "ከእጦት የተገኘ ማንነት" ስትል የሰው ልጅ ሙሉ የሚሆነው ደስታንና ስኬትን ብቻ በመሰብሰብ ሳይሆን፣ በልምምድ ውስጥ በሚያጋጥሙት ክፍተቶችና "እጦቶች" ጭምር መሆኑን ትጠቁማለች።    ✍️ በዚህ ግጥም ውስጥ "ጥቁር እና ነጩን እያደበላለቅሽ" የሚለው መስመር የሕይወትን ተቃራኒ ገጽታዎች:- ብርሃንና ጨለማን፣ ደስታንና ሃዘንን በአንድነት መሳልን የሚያሳይ ሲኾን ሕይወት በአንድ ቀለም ብቻ የምትጻፍ አለመኾኗንና በእነዚህ ተቃራኒዎች መጋጨትና መዋሃድ ውስጥ የምትፈጠር  እንደሆነች ይገልጻል።    ✍️ "በውልደትሽ ስቄ፣ በሞትሽ ማልቀሴ ሰው አርጎኝ አለፈ" የሚለው ስንኝ፣ እውነተኛ "ሰውነት" የሚገኘው በሁለቱም የሕይወት ጫፎች ውስጥ በማለፍ እንደሆነ ያስረዳል። ገጣሚዋ ሳባ ሲሳይ በዚህ ግጥሟ ውስጥ ስቃይና ሃዘን ውድቀት ብቻ ሳይሆኑ የ"ሰው መሆኛ" ሂደቶች መኾናቸውን ታመሰጥራለች። ​   ✍️እንደአጠቃላይ ይህ ግጥም በሐዘንና በደስታ መካከል ያለውን ቀጭን የውህደት መስመር የሚያሳይ፣ ረቂቅ ጥበባዊ ዕይታ ያለው ሥራ ነው። የሳባ ስንኞች ቅምሻ (2) (እጣ እና ጎዳና) ውልግድግድ አይደለም የሁሉ ሰው መንገድ የአንዳንዱ ቀና ነው፣ ወዴት አለች? ብሎ የሲኦል አቅጣጫ እግሩን ቢጠቁመው፣ በጓሮ በኩል ነው ገነት የሚገባው። ገጽ 15 ✍️ሳባ በዚህ ግጥሟ ውስጥ "እጣ" እና "መንገድ" ያላቸውን ረቂቅ ግንኙነት በሚገርም ምልከታ ትፈትሻለች። በሰዎች ዘንድ "ቀና መንገድ" የሚባለው ነገር እንደየግለሰቡ ዕድል የሚለያይ መሆኑን በአመሥጥሮ ታስረዳለች። ​የዚህ ግጥም በጣም አስገራሚው ክፍል "በጓሮ በኩል ነው ገነት የሚገባው" የሚለው ስንኝ ላይ ይገዝፋል። እዚህ ላይ የእጣ ፋንታ ኃይል በአያሌው ተመሥጥሯል። አንድ ሰው በገሃዱዓለም ወደ ጥፋትና ውድቀት የሚወስድ መንገድ ላይ የቆመ ቢመስልም፣ እጣ ፋንታው "ቀና" ከሆነ ባልታሰበ አቅጣጫ እግሩ ወደ መልካሙ ስፍራ ሊያደርሰው እንደሚችል ያሳያል። ​አንድም በሌላ አመሥጥሮ ሲታይ "እግር የጠቆመው አቅጣጫና ትክክለኛው መድረሻ ላይገጣጠሙ ይችላሉ።" የሚል አሥረጅነት አለው። ሳባ በዚህ ግጥም ውስጥ "የእጣ ፋንታ ኃይል" ከሰው ጥረት እና የሕይወት ሩጫ በላይ መሆኑን የሚገልጽ ፍልስፍና ያዘለ ጥበባዊ ዕይታዋን ያስቀመጠች ሲኾን ​በአጠቃላይ ግጥሙ "ሰው በሄደበት መንገድ ብቻ ሳይሆን፣ በእጣው ፋንታው የኃይል ስፍር ልክ ይደርሳል" የሚል ምሥጢር አለው። የሳባ ስንኞች ቅምሻ (3) (የሀገሬ እብዶች) ጥንትም ያገሬ ሰው ዛሬም ያገሬ ሰው ነገም ያገሬ ሰው አንድ ነው እብደቱ፣ ድንኳኑን በሞላ ሰርግ ነው ማለቱ። (ገጽ 76) ሳባ በእነዚህ ስንኞች ውስጥ የኢትዮጵያን ማኅበራዊ ሥነ-ልቦና በአንድ ትልቅ ምስል (ሜታፎር )የገለጠችበት መንገድ እጅግ አስደናቂ ነው። ገጣሚዋ "እብደት" የሚለውን ቃል የተጠቀመችው ለስድብ ሳይሆን፣ ያለንበትን ተጨባጭ ሁኔታና የሕዝቡን የጋራ ጠባይ ለመግለጽ ይመስላል። በዚህ ​ግጥም ልንረዳው የምንችለው ነጥብ፦ ​1. የማይለወጥ ማንነት ​"ጥንትም ያገሬ ሰው ... ዛሬም ያገሬ ሰው... ነገም ያገሬ ሰው አንድ ነው እብደቱ" ​ገጣሚዋ (ያለፈውን፣ የአሁኑንና የወደፊቱን) ጊዜ በአንድ መስመር በማገናኘት፣ የሀገሯ ሰው ባህሪ እንደማይለወጥ በድፍረት ትናገራለች። ይህ "አንድ ዓይነት እብደት" ትውልድ ተሻጋሪ መሆኑንም ታሳያለች። ​2. የ"ድንኳን" ተምሳሌት ​"ድንኳን" በሀገራችን ባህል ለሁለት ትልልቅ ነገሮች ይጣላል፦ ለሰርግ ወይም ለለቅሶ። እዚህ ጋር ገጣሚዋ ያስቀመጠችው ​"ድንኳኑን በሞላ ሰርግ ነው ማለቱ" ​የሚለው መስመር የግጥሙ ቁልፍ ነው ማለት ይቻላል። ድንኳኑ ለለቅሶ ቢሆን እንኳን፣ የሀገሬ ሰው ግን "ሰርግ ነው" ብሎ ያምናል ወይም ራሱን ያሳምናል ትለናለች። ይህንን በሁለት መንገድ ማየት ይቻላል፦ ✍️​እንደ ጥንካሬ፦ በችግርና በለቅሶ ውስጥም ቢሆን ደስታን የመፈለግ፣ ተስፋን የማለምና የጭንቅን ጊዜ በፈገግታ የማለፍ ድንቅ አቅም ተችሮታል እንደማለት ሲኾን ✍️እንደ ድክመት:- ደግሞ ያለንበትን መከራና የለቅሶ ድንኳን አውቀን ለመለወጥ ከመጣር ይልቅ፣ ሁሉንም እንደ ደስታና እንደ ሰርግ እያየን እውነታውን የመሸሽ  ዝንባሌ እናሳያለን  እንደማለት ይመስላል። ​ባጠቃላይ፦ ግጥሙ የሀገራችንን ሕዝብ ተስፋ የመቁረጥና የመጽናት ምሥጢር በምጸት ይገልጻል። ገጣሚዋ በዚህ ግጥም ውስጥ የጠቀሰችው እብደት መከራን ወደ ደስታ የመቀየር "ቅዱስ እብደት" ወይም ደግሞ ችግርን ያለማስተዋል "የግድየለሽነት እብደት" ሊሆን ይችላል። የሳባ ስንኞች ቅምሻ (4) (እንዴ!) ... እንኳን እምነት ጠፋች እንኳን ተሰወረች ትሂድ ትሽሽ ትራቅ የትም ዓለም ትድረስ፣ እግዜር ያነገሠው የማስተዋል መንፈስ እኪገዛን ድረስ። (ገጽ 72) ሳባ "እንዴ" በሚለው የግርምት ርእስ በያዘው በዚህ ግጥሟ  በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ስለሚኖሩ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች (እምነት እና ማስተዋል) ያለውን ግጭትና ቅደም-ተከተል በድፍረት ትመረምራለች። ​ "እንዴ!" የሚለው ርዕስ በራሱ የአግራሞት ቃል ነው። ምናልባትም ሰዎች እምነት ጠፋ ብለው ሲደነግጡ፣ ገጣሚዋ ግን "እንዴ! ማስተዋል ሳይኖረን እምነት ቢኖረን ምን ዋጋ አለው?" የሚል ተቃራኒ ምላሽ እየሰጠች የሚመስል ነገር አለው። ​"እግዜር ያነገሠው / የማስተዋል መንፈስ እኪገዛን ድረስ" ​እዚህ ጋር ገጣሚዋ ትልቅ "ፍርድ" ትሰጣለች። ያለ ማስተዋል የምትኖር እምነት ለሰው ልጅ አደጋ ወይም ባዶ ልትሆን እንደምትችል ታመላክታለች። ፈጣሬ ራሱ በሰው ውስጥ የሰጠው ትልቁ ጸጋ "ማስተዋል" መሆኑንና፣ ይህ የማስተዋል መንፈስ በሰው ልጅ ላይ ንጉሥ ሆኖ ካልተገለጠ፣ ዝም ብሎ ማመን ብቻውን ዋጋ እንደሌለው ትገልጻለች። ​ባጭሩ፦ ግጥሙ "ከጽልመታዊ እምነት፣ ብርሃናዊ ማስተዋል ይቀድማል" የሚል መልዕክት አለው። እምነት እንኳን ብትጠፋ፣ የማስተዋል መንፈስ እስካለን ድረስ ወደ ትክክለኛው መንገድ መመለስ እንደምንችል ተስፋ ይሰጣል። ​ የሳባ ስንኞች ቅምሻ (5) (ዘመንና ሰው) ዘመን ቀድሞኝ ሲከንፍ ከፊት ፊቴ ሲበር፣ እሱን በመከተል እኔ የተጓዝሁት ወደመጣሁበት ወደኋላ ነበር። (ገጽ 67) ✍️እነዚህ ስንኞች በውስጣቸው ጥልቅ የሆነ የፍልስፍና ጥያቄን ተሸክመዋል። ገጣሚዋ በዘመን እና በሰው መካከል ያለውን ተቃርኖ (Paradox) እጅግ በሚገርም ምስል ከስታ አቅርባዋለች። ዘመን ወደ ፊት ሲሮጥ፣ ሰው ግን በዘመኑ ትይዩ ወደ ኋላ እየተጓዘ መኾኑን ለማሳየት ስትጥር እናያታለን። ​ዘመን ሁልጊዜም ወደ ፊት ይከንፋል። ሰው ግን ያንን ዘመን ለመከተል በሚያደርገው ሩጫ ውስጥ፣ በዕድሜ እየገፋ ሲሄድ የሚቀርበው ወደ መጪው ጊዜ ሳይሆን፣ ወደ መጣበት (ወደ መሬት ወይም ወደ አለመኖር) እንደሆነ ጥቁምታ ትሰጣለች። ​በሌላ በኩል ደግሞ፣ ዓለም በቴክኖሎጂ እና በጊዜ ወደ ፊት ስትገሰግስ፣ የሰው ልጅ ግን በባህሪው እና በስብዕናው ወደ ኋላ እየተመለሰ መሆኑን የሚገልጽ የቁጭት ድምፅ እያሰማችም ይመስላል። ​"እኔ የተጓዝሁት ወደ መጣሁበት ወደኋላ ነበር" ​ይህች ስንኝ ብቻዋን በሁለት ትርጉሞች ልትመሠጠር ትችላለች። 1- የሰው ልጅ በተ​ፈጥሮ መንገድ ከማኅፀን ወጥቶ ወደ መቃብር (ወደ አፈር) መመለሱን ለማጠየቅ። ​2- ዘመን በገፋ ቁጥር የሰው ልጅ በሐሳቡ ይበልጥ ወደ ኋላው (ወደ ትላንትናው) በትዝታ እንደሚመለስ ለማስረዳት። ​ባጭሩ፡ ሳባ ሲሳይ በእነዚህ ስንኟቿ ዘመን ሲሮጥ እኛ ግን የምናረጀውና የምንመለሰው ወደ ኋላ መሆኑን በማሳየት፣ የሕይወትን አጭርነትና ግራ አጋቢነት በሚያምር ጥበባዊ ሐተታ ትገልጻለች። ​ የሳባ ስንኞች ቅምሻ (6) (የነገሥታት ሽፍጠት) ውሸት እያሳዩን እውነት ነው ብላችሁ ይሉናል መሥክሩ፣ በስንዴ ማሳ ውስጥ ሂዱ እንክርዳድ ዝሩ፣ ጎጆ ለሚናፍቅ መቃብር ቆፍሩ፣ ይሉናል ነገሥታት ይሉናል መንግሥታት ነፍጥ እያስነገቡ በትክሻችን ላይ፣ ዙፋን ተሸክመን ባቀረቀርን ልክ ከፍታን እንዳናይ። (ገጽ 47) ገጣሚዋ ሳባ በዚህ ግጥም ውስጥ በስልጣን እና በጭቆና መካከል ያለውን ግጭት፣ እንዲሁም የአምባገነንነትን ባህሪ በምስል ከሳችነት ትገልጻለች። "የነገሥታት ሽፍጠት" የሚለው ርዕስ ራሱ ገዥዎች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የሚያደርጉትን የተንኮልና የታማኝነት ጉድለት የሚያሳይ ነው። ​የግጥሙን ይዘት በሦስት ዋና ዋና ነጥቦች ከፍለን ብናየው፦ ​፩. የሐሰት ምስክርነትና የግብረ-ገብነት ውድቀት ​ገጣሚዋ "ውሸት እያሳዩን እውነት ነው ብላችሁ ይሉናል መሥክሩ" በማለቷ ውስጥ የሀገር መሪዎችና ሹማምንት እውነታውን በማጣመም ተመሪውን ሕዝብ በውሸት ዓለም ውስጥ እንዲኖር የሚያደርጉበትን ጫና ግልጽ አድርጋ ታሳያለች። "በስንዴ ማሳ ውስጥ ሂዱ፤እንክርዳድ ዝሩ" በሚለው ስንኝ ደግሞ ነገሥታት ለዙፋናቸው እድሜ መራዘም ሲሉ አዎንታዊና መልካም በሆነው ነገር ላይ ጥፋትን እንዲዘሩ የሚታዘዙ መልእክተኞች እንዳሏቸውና ሥልጣን የአጥፊነት ካባን እንዳጎናጸፋቸው ትገልጻለች። ​፪. የሃይልና የጉልበት አገዛዝ ​"ነፍጥ እያስነገቡ በትክሻችን ላይ..." ​ይህ ስንኝ ሕዝቡ በራሱ ትከሻ ላይ ለራሱ ስቃይ የሚሆንን መሳሪያ (ነፍጥ) እንዲሸከም መገደዱን ያሳያል። ጭቆናው የሚከናወነው በተጨቋኙ ሕዝብ ጉልበት እና ትክሻ እንደሆነና መሪዎች  ዙፋናቸውን የሚያጸኑት በሰላማዊ መንገድ ሳይሆን በሃይል እንደኾነ ይጠቁማል። ​፫. ያቀረቀረ ትውልድና የዙፋን ከፍታ ​"ዙፋን ተሸክመን ባቀረቀርን ልክ ከፍታን እንዳናይ" ​እዚህ ስንኝ ላይ ኹለት ትልልቅ መልእክቶች አሉ። አንደኛው፣ ተገዥው ሕዝብ የገዥዎችን ዙፋን ተሸካሚ መሆኑና የመሪዎችን ሥልጣን ለማርዘም እንደመሣሪያ ማገልገሉ ሲኾን ሁለተኛውና ዋናው ነጥብ ግን፣ ዙፋንን መሸከም፣አምባገነን መሪዎችን አሜን ብሎ መቀበል በተሸናፊነት ስሜት ማቀርቀርን የሚሚጠይቅ ነው የሚለውን ነጥብ ያስረዳል አንድ ሕዝብ እንደሕዝብ የመሪዎችን ዙፋን ተሸክሞ ሲያቀረቅር ደግሞ ዓይኑ ወደ መሬት  ታች ታቹን ብቻ ስለሚያይ ከፊቱ ያለውን "ከፍታ" ወይም ነፃነት ማየት አይችልም። ከፍታን ለማየት ቀና ማለት ያስፈልጋል፤ ዙፋን የተሸከመ ትክሻ ደግሞ ቀና ለማለት አይመቸውም። የሚል አመሥጥሮ አለው። ​ባጠቃላይ፦ ግጥሙ ሥልጣን እንዴት የሰውን ልጅ ክብርና ነፃነት እንደሚሰርቅ፣ ግነት በሌለውና በረቀቀ ስላቅ የሚያመሠጥር የፖለቲካና የማህበራዊ ሂስ ውጤት ነው። የሳባ ስንኞች ቅምሻ (7) (የተለይ ወግ) ... እንገናኛለን ይላል በሙሉነት ሞትን ሳይጠረጥር መቅረትን ሳያህል፣ ሁሉ መንገድ ወስዶ ይመልስ ይመስል። (ገጽ 61) ✍️​ሳባ በእነዚህ ስንኞቿ ውስጥ የሰው ልጅ የኑባሬ "ሙሉነት" እና መተማመን ላይ ትራቀቃለች። "​ሰው "እንገናኛለን" ብሎ ሲቃጠር ወይም ሲለያይ፣ በውስጡ ምንም ዓይነት ያለመገናኘት ጥርጣሬ የለውም። ያንን መለያየት እንደ ጊዜያዊ ፋታ እንጂ እንደ መጨረሻ አያየውም።" የሚለው ሐተታ የገጣሚዋ ትዝብት ነው። "​በሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስጥ ሞት አይቀሬ እውነት ቢሆንም፣ የዕለት ተዕለት ኑሯችን ግን ሞትን የረሳ ይመስላል" በማለት ትታዘባለች። ሳባ ​"ሞትን ሳይጠረጥር"፦ በሚለው ግጥማዊ ሐረግ ውስጥ "ሰው ለመገናኘት የነገ ቀጠሮ ሲይዝ ለሞት ዕድል አይሰጥም" የሚል ሐተታ አስቀምጣ እናገኛታለን። ​"መቅረትን ሳያህል"፦ በሚለው መስመር ውስጥ "ቀጠሮው ሳይሳካለት ሊቀር እንደሚችል እንኳን ከግምት ውስጥ አያስገባም" የሚል እይታዋን ታጋራለች። ከኹሉም በላይ ደግሞ ​"ኹሉ መንገድ ወስዶ ይመልስ ይመስል" የሚለው መስመር እጅግ ጥልቅ ምሥጢር ተሸክሞ ቆሟል። "በሰው ልጅ እሳቤ፣ መንገድ ኹልጊዜ "ኹለት አቅጣጫ" (መሄጃና መመለሻ) አለው። ነገር ግን የሕይወት መንገድ አንድ አቅጣጫ ብቻ መሆኑንና ሄዶ መቅረት፣ ተራምዶ አለመመለስ እንዳለ ዘንግተነዋል።" የሚለውን ሐሳብ እዚህ ስንኝ ላይ አጉልታ አስቀምጣለች። የሳባ ስንኞች ቅምሻ (8) (እንደ አምሥቱ ቆነጃጅት) ዘይቴ አልቆብኝ ብወጣ ለመግዛት፣ ያ ሁሉ ጥበቃ ከሸፈ በቅጽበት፣ ለካስ ጉዞ አይደለም የኹሉ ሰው ብልጫ፣ ፍጻሜ ነው ገድል ፍጻሜ ነው ዋንጫ። (ገጽ 56) ሳባ በዚህ ግጥሟ ውስጥ በወንጌል ላይ የተጠቀሰውን የአምስቱ ሰነፍ ቆነጃጅት ታሪክ እንደ ማነጻጸሪያ በመጠቀም፣ የሰው ልጅ በምድራዊ ሕይወቱ ሊኖረው ስለሚገባው ዝግጁነት በምስል ከሳች ቋንቋ ትገልጻለች። ​የዚህን አጭር ግጥም ዋና ዋና ጭብጦች አውጥተን  ብንተነትን 3 ዋና ዋና ነጥቦች እናገኛለን፦ ​፩. የዝግጁነት አስፈላጊነት ​"ዘይቴ አልቆብኝ ብወጣ ለመግዛት" የሚለው ስንኝ፣ ነገሮች ከረፈዱ በኋላ የሚደረግ ጥረት ዋጋ እንደሌለውና በሕይወት ጉዞ ውስጥ ለታላቁ የፍጻሜ ቀን አስቀድሞ መዘጋጀት እንጂ ከረፈደ በኋላ የሚደረግ መሯሯጥ በሕይወት ላይ የትርጉም ለውጥ እንደማያመጣ ይገልጻል። ​፪. የጥበቃ ትርጉም ​"ያ ሁሉ ጥበቃ ከሸፈ በቅጽበት" የሚለው መስመር፣ አንድ ሰው ለረጅም ጊዜ የለፋበትና የጠበቀው ነገር የዝግጁነት ማነስ በፈጠራት አንዲት ትንሽ ስህተት ምክንያት ሊበላሽ እንደሚችል ይጠቁማል። ​፫. ጉዞ እና ፍጻሜ ​ለካስ ጉዞ አይደለም የሁሉ ሰው ብልጫ፣ ፍጻሜ ነው ገድል ፍጻሜ ነው ዋንጫ። ​እነዚህ ስንኞች ላይ ገጣሚዋ ትኩረታችንን ከሂደቱ ወደ ግብ ታዞረዋለች። ብዙ ሰው አብሮ ይጓዛል፣ አብሮ ይደክማል፤ የፍጻሜው ጫፍ ላይ የድልን አክሊል የሚቀበለው ግን ጉዞውን የጀመረው ሁሉ  ሳይሆን፣ እስከ መጨረሻው በጽናት በድል መንገዱን የጨረሰው ብቻ ነው። "ገድል" የሚባለውም በመንገድ ላይ የታየው ጥረት ሳይሆን፣ በፍጻሜው ላይ የሚገኘው ውጤት መሆኑን አስምራ ታመሠጥራለች። ባጠቃላይ ፦ ይህ ግጥም ሕይወት የሩጫ ውድድር እንደሆነችና ዋናው ቁም ነገር ደግሞ መጨረሻው ላይ በድል መገኘት መሆኑን የሚያሳስብ  ድንቅ ስራ ነው። ማጠቃለያ እንደአጠቃላይ የሳባ ስንኞች:-    ✍️የግጥም አጻጻፍ ጥበብን የተላበሱ    ✍️ቤት አመታታቸው ያልከሸፈ    ✍️የስንኝ አመጣጠናቸው ያልተዛነፈ    ✍️ምትና ዜማቸው ለቀለምና ለቃል ስብራት ያልተጋለጠ    ✍️በቃላት ምርጫ ውበታቸው ያልረገፈ    ✍️የዘይቤ አጠቃቀማቸው ከፍ ያለ    ✍️የሐሳብ አወራረዳቸው የሰመረ    ✍️የምናብ ኃይልና የምስል ፈጠራ ሂደታቸው የረቀቀ በሳል ሥራዎች ናቸው።    ✍️ከይዘትና ከጭብጥ አንጻር ከማኅበረሰቡ ተቀድተው ለማኅበረሰቡ የቀረቡ፤ሥጋዊ ፍራቻ ሳያሽኮረምማቸው የሕዝቡን ክፍተት ለሕዝብ፣የመንግሥትን ክፍተት ለመንግስት፤የአምላክንም ክፍተት ለአምላክ (ሎቱ ስብሐት )በድፍረት የገለጡ፤የባህል እና የሐይማኖት ተጽእኖ ሳይጫናቸው በነጻነት ስለኹሉም ማኅበራዊ ጉዳዮቻችን ሂስ ሰጥተው ያለፉ፤ የሚያልፉ፤የማያልፉ የጥበብ ሥራዎች ናቸው። በመጨረሻም :- ሳባ ሲሳይ በ"ብርሃን ጥሞና" የግጥም ስብስብ ሥራዋ የተሳካላትና አሰላሳይ ባለምናብ ገጣሚት መኾኗን ያሥመሰከረች ጀግና ገጣሚት ናት የሚለውን ምሥክርነት በልበ ሙሉነት እየሰጠሁ በመጽሐፏ መግቢያ ላይ ስለግጥም ጽንሰ ሐሳብ ባሰፈረችው የራሷ ጽሑፍ ዳሰሳዬን እቋጫለሁ። ሳባ ሲሳይ በዚህ መጽሐፍ መግቢያ ላይ እንዲህ ትላለች። "አንድ ጥሩ ሥዕልና አንድ ጥሩ ግጥም የአንድ ክፍለዘመን ምርምር ናቸው። ከተጻፉ በኋላ ይጻፋሉ፤ከተሣሉም በኋላ የተመልካቾቻቸውን አሻራ እየተቀበሉ ይሣላሉ።" //ይቆየን// ሐዋዝ የሻነህ ሚያዝያ ፳፻፲፰ ዓ.ም
Comments (3)
Geremew Tsegaw May 14, 2026 · 09:27
Great.
Waka Books May 14, 2026 · 11:05
Thank you for sharing your review.
Waka Books May 14, 2026 · 11:05
Thank you for sharing your review.
Login to leave a comment.
ሐዋዝ የሻነህ
1 reviews · 2 followers
View All Reviews
Have you read this book?

Share your own review and help the community.

Write a Review