All Reviews
Book cover
መጽሐፈ ሚርዳድ

by ግሩም ተበጀ

5.0 avg · 1 review
T
Tsegaw Mamo
2 reviews · 0 followers · September 9, 2026
5/5

የሌላ ሰማይ ኮከብ

❝የሌላ ሰማይ ኮከብ ❞ ~~~~~~~~~~~ √ የመጽሐፉ ርዕስ :- መጽሐፈ ሚርዳድ √ የመጽሐፉ ዘውግ :- ፍልስፍናዊ ልቦለድ √ የመጽሐፋ ደራሲ:- ሚካኤል ኔይሚ √ተርጓሚ :- ግሩም ተበጀ √ የገጽ ብዛት :- 249 √የኅትመት ዘመን :- 1948 ********* ❝በዓለማችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ መጻሕፍት አሉ። መጽሐፈ ሚርዳድ ግን ከሁሉም ይልቃል።ሌሎች መጽሐፍት ሁሉ የተጻፉ ናቸው። መጽሐፈ ሚርዳድ ግን እንደሌሎች መጻሕፍት የተጻፈ ሳይሆን ተረግዞ የተወለደ ነው ❞ ይላል ኦሾ ********* ¶ ስለ ጸሐፊው ¶ ሚካኤል ኔይሚ በሊባኖስ በባስኪንታ ተራራ ስር በ1889 የተወለደ ሲሆን በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከተነሱ ምርጥ ሦስት የአረቡ ዓለም ጸሐፊዎች አንዱ ነው ።ሚካኤል ኔይሚ ከግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተሰብ የተወለደ ፣ የሂንዱይዝም ፣ የቡድሂዝም እና የአስልምና ሱፊ አድናቂ የነበረ ፤ የሩሲያ እና የአንግሎ ሳክሰን ሥነ ጽሑፍ ተጽእኖ ያረፈበት፤ እጅግ ተወዳጅ ገጣሚ ፣ ፈላስፋ እና መንፈሳዊ ደራሲ ነው ። በአሜሪካ በነበረበት ወቅት ከነ ካህሊል ጅብራን ጋር በመሆን New york pen league የሚል ማኅበር በመመስረት ለአረብ ሥነ ጽሑፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን በ1948 "ሚርዳድ" መጽሐፍን በሊባኖስ በማሳተም ከፍተኛን ዝና ያተረፈ ዘመናዊ ደራሲ ነው። ¶¶ መግቢያ¶¶ መጽሐፈ ሚርዳድ :-ምድር ላይ ተከታይና ተቋም የሌለው የሃይማኖት መጽሐፍ የሚመስል ሲሆን ...ሰው ሌላ ማንነት እንዳለው ፣በውስጣችን ያለውን መለኮታዊ አቅም በማውጣት የአካልን እና የነፍስን ሁለትነት አጥፍተን በነጻነት በሙላት ፣ ሞትን ተሻግረን ለዘላለም እንድንኖር የሚሰብክ... ጽንፍ ዓለሙንና የሰውን ልጅ እንደገና በሌላ ዐይን እየተመለከተን ሌላ ያልተኖረ ውብ ዓለም እንዳለ የሚጠቁም ድንቅ የተማሕልሎ(Mystical )ፍልስፍናዊ መጽሐፍ ነው። ስለ ሕይዎት ፣ ስለ ነፍስ ፣ ስለ ፍቅር ፣ ስለ ሞት ፣ ስለ ዝምታ ፣ ስለ ሀብት ።፣ስለ እኔነት ፣ስለ አምላክ ባሕሪ ፣ ስለ እውነት ስለ ተፈጥሮ ፣ ስለ መንፈሳዊነት ወዘተ በአካልና ከአካል ባሻገር በጥልቀት የሚመለከት መጽሐፍ ነው ።መጽሐፉ በስሜት መነካት ጭምር ተደጋግሞ መነበብ ያለበት የምሥራቃውያን ፍልስፍናን የያዘ ሰላማዊ መጽሐፍ ነው። ~~~~~~~~~~~~~ √√ መጽሐፉ የተመሰረተበት አጽም እንዲህ ነው። ኖኅ ከነ ቤተሰቦቹ እና "ከመርከቡ ሾልኮ ገቢ ሰው" ጋር 9 ሆኖ ከጥፋት ውሀ በኋላ መርከቧ ባረፈችበት ተራራ ላይ ገዳም መስርቶ ይኖር ነበር ። ገዳሟን ከነ ሥርዓቷ ለልጁ ለሴም አወረሰው ።ኖኅም ሴምን እንዲህ አለው :- 'ቁጥራችሁ ከ9 አይጉደል አንድ ሰው ሲሞት እግዚአብሔር ሌላ ይተካል አለው' ። ተረኩ ይጠርና አንድ የተጎሳቆለ ምስኪን ሰው መጥቶ ገዳሙ ውስጥ አስገቡኝ እያለ ይማጸናል ...የገደሙ አበምኔት ግን አልፈቀደለትም ነበር ... ነገር ግን ከ7 ዓመታት ደጅ ጥናት በኋላ ምስኪኑ ሰው ኃያል ሰው ሆኖ የታላቁ ገዳም አበምኔት ሆነ ። የዚህ መጽሐፍ ደራሲም የዚህን ሰው እና ገዳም ዝናውን በተረክ ሰምቶ እጅግ አስቸጋሪውን ፤ በፈተና የተሞላውን የባልጩት የተራራ አናት ላይ ከወጣ በኋላ አረፍ እንዳለ እንቅልፍ ወሰደው ። የማይታወቅ ጊዜ እንደተኛ አንድ ለስላሳ እጅ ነካውና ነቃ ❝ ደብዛዛ ፋኖስ በእጇ የያዘች ቆንጆ ኮረዳ ፊቴ ቆማ አየሁ ።ሙሉ ለሙሉ እርቃኗን ነች" ... ኦህ የተራራው ጫፍ ነጻነት !...የኮረዳዋ ውበት! ከዚህ አንጻር ሌላው ሁሉ እንዴት ተራ ነው! እነርሱን ብላ ነፍሴ ራሷ ጥላኝ ጠፍታለች❞ይላል። ይኸን ሰው ...ሻማዳም (የውሸት ሰው) አገኘውና እንዲህ አለው " ታትሞ ዓለም ያነበው ዘንድ ፣የተቀደሰውን መጽሐፍ የምሰጠው የተባረከ ሰው " አንተ ነህ አለው ። ጸሐፊውም ግብዣውን ተቀብሎ የታላቁን አበምኔት የሚርዳድን መጽሐፍ ጻፈ። ~~~~~~~~~ የመጽሐፉ ዋና ተዋናይ "ሚርዳድ " የተባለው የገዳሙ አበምኔት ሲሆን ለ8ቱ ደቀ መዛሙርት ስለ ጽንፈ ዓለሙ እና ሰው በሌላ ዐይን እየተመለከተ ባልተለመደ ጆሮ አንዲሰሙት በውብ ቋንቋ በ37 ምዕራፎች በመናገር መጽሐፉን ጽፎ ይጨርሳል። መጽሐፈ ሚርዳድ በገዳሙ አበምኔት ስም የተሰየመ የአበምኔቱ ትምህርት ነው ። መጽሐፉ በአብዛኛው ደቀ መዛሙርቱ "ሚርዳድን " የተለያየ ጥያቄ እየጠየቁት መልስ የሚሰጥበት ነው ።ባጠቃላይ ነፍስን ከድባቴዋ የሚቀሰቅስ ወደ ሙላት የሚወስድ ሕይዎታዊ የተማህልሎ (Mistical) መጽሐፍ ነው ። ~~~~~~~~~ ¶¶ደቀ መዛሙርቱ ስለ ሚርዳድ ሲመሠክሩ¶¶ ገዳሙ ውስጥ አብረውት የሚኖሩት ደቀ መዛሙርት በምዕራፍ 6 (ሥድስት) ላይ እያንዳንዳቸው መምህራቸውን ሚርዳድን እንዲህ ገልጠውታል። " የሌላ ሰማይ ኮከብ ነው ፣ቅኝቱን ያላወቅነው ግሩም በገና ነው ፣ ዘውድ የሚያልም ለማኝ ነው፣የመርከቧ ሾልኮ ገቢ ነው፣ በተቃርኖ ውስጥ የጠፋ ታላቅ አእምሮ ነው ፣ወዳጅ ጆሮ የሚሻ ተንከራታች ልሳን ነው "ወዘተ እያሉ በየተራ ስለ እርሱ ምሥክርነታቸውን ይሰጣሉ። ይኸ የሚያመላክተው መጽሐፉ ለዚህ ዓለም ሰዎች አዲስ እንግዳ መሆኑን ነው ። የማናውቀው ሰማይ ኮከብ ፣ ቅኝቱን ያላወቅነው በገና ፣ የኖኅ መርገብ ውስጥ የገባ የማናውቀው ሌላ ሰው ለእኛ ምናችን ነው ? በአሁኑ ዐይናችን ማየት የማንችለው በአለን ጆሮዋችን የማንሰማው ሰው የተናገረው መጽሐፍ ነው። ሚካዮን የሚባለው ገዳማዊ ደቀ መዝሙር ሚርዳድን"ማን እንደሆንክ አትነግረንም ? ብሎ ጠየቀው ። ሚርዳድ እንዲህ ብሎ ይመልስለታል ❞... ውስጡ ሁለንተናን የያዘን ሰው የቱስ ሀገር ችሎ ይይዘዋል? አያት ቅድመ አያቱ እግዜር የሆነ ሰው ፣ማንንስ ዘመዴ ሊል ነው?❝ በማለት በመጽሐፉ ውስጥ "ሰው በመታቀፊያ ውስጥ ያለ እግዜር ነው" "ሰው የእግዜር ቅዱስ ነጻነት ወራሽ ነው " እያለ የነገራቸውን አይነት ልውጥ ማንነት እንዳለው ይመልስለታል ። ሰው ወሰን አልባ ማንነት እንዳለው እና እሱም እንደሆነው ይናገራል ። በእርግጥም እንደዚህ ያሉ ሰዎች በእውኑ ዓለም እንዳሉ ይነገራል። ¶¶ ስለ አመክንዮ ¶¶ ስለ አመክንዮም (logic) እንዲህ ይናገራል። "አመክንዮ ሲያድግ እምነት ይሆናል " አመክንዮ ለሰንካላው መደገፊያ ከዘራ ነው ፤ ለባለፈጣን እግሩ ግን ሸክም ነው ፣ ለባለክንፋሙ ደግሞ እጅጉን የባሰ ሸክም ነው ።አመክንዮ ያረጀ እምነት ነው ፣ እምነት የበሰለ አመክንዮ ነው" በማለት አመክንዮ (logic) የደካሞች እና የሰነፎች ምርኩዝ ከዘራ እንደሆነ ይናገራል። ይቀጥልና በገጽ 228 ላይ "ንዑስ እግዜር አይታገድም ይኸንን ዝቅተኛ ሰዎች "ደመ ነፍስ" ሲሉት ተራ ሰዎች ደግሞ አመክንዮ ይሉታል ፣ የላቁ ሰዎች ደግሞ የነብያት ራእይ ይሉታል ፣ አንዳንዶች መንፈስ ቅዱስ ይሉታል ሚርዳድ ግን ሥም የለሽ ኃይል ይለዋል " በማለት ይናገራል። በሰዎች ውስጥ ያለውን ንዑስ እግዜርን "አመክንዮ " የሚሉት ዝቅተኛ ሰዎች ናቸው ማለቱ ታላላቅ ሰዎች ግን ይኸን ዓለም የሚያውቁበት በራእይ ፣ በመንፈስ ቅዱስ ወይም በሌላ ኃይል እንደሆነ እየነገረን ነው ። ¶¶ ስለ ታላቁ ናፍቆት ¶¶ ሚርዳድ ስለ ታላቁ ናፍቆት እንዲህ አለ "ታላቁ ናፍቆት ከልብ መንጭቶ ልብን ይጋርዳል ...ሀገሬ የሚለው፣ የሚዘምርለት ምድር የለውም፣ የልቡ ዓይን የወዲያኛው የወንዙ ዳርቻ ላይ ነውና... የነቃ በሚመስለው ዓለም መሃል የእንቅልፍ ልብ ተጓዥ ነው...ታላቁ ናፍቆት ያልነካቸው ጉድጓዶቻቸውን ቆፍረው እዚያ ውስጥ ኖረው ፣ ተራብተው ፣ መሞት በቂያቸው ነው " የነጻ አየር እና የፅንፍ የለሽ ሰማይ ናፋቂ..." የታላቁ ናፍቆት ተቋዳሾች ምነኛ ዕድለኞች ናቸው ። ታላቁን ናፍቆት መረዳት የጀመሩ ብፁዓን ናቸው እላለሁ። ~~~~~~~~ ¶¶ ሚርዳድ ስለ ዝምታ ሲናገር¶¶ " የጸጥታን የማይረታ ሰላም ያወቀን ሰው ማንም አይረብሸውም ፣ ማንንም አይረብሽም...ንግግር ቢበዛ ታማኝ ውሸት ነው። ፀጥታ ቢበዛ እርቃን እውነት ነው .."ባልደሰቦቼ ሆይ ፣ የሚያስካካን በጎ ምግባር ፍሩ ፣ ውርደታችሁን እንዳፈናችሁት ሁሉ ክብራችሁንም እንዲሁ አፍናችሁ ያዙት ። የሚያስካካ ክብር ጸጥ ካለ ውርድት ይከፋልና ፣ ሆይ ሆይታ የበዛበት በጎነት ከጋግርታም ክፋት ይከፋልና ..." ገጽ 95 በማለት ለውዳሴ እና ሙገሳ የሚፈጠኑትን በጎ አድራጊዮች ተችቷል ። ዝምታ ጥልቅ ሰላም እንደሆነ ይናገራል። ~~~~~~ ¶¶ሚርዳድ ስለ ፍቅርም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ይላቸዋል¶¶ "ፍቅር በሕይዎት ማራኪ ዜማ የሚደንስ ሰላም ነው ..."ፍቅር የእግዚአብሔር ሕግ ነው ፣ "የምትኖሩት ፍቅርን ትማሩ ዘንድ ነው "..የሚያስር ፍቅር ፍቅር "አይደለም ይልቁንስ ከእስር ነጻ የሚያወጣ ብቸኛው ነገር ፍቅር ነው ።ሁሉንም ስትወድ በምንም አትታሰርም። ...አፍቃሪውን የሚያስገብር ፍቅር ...ፍቅር አይደለም። ሥጋና ደም የሚበላ ፍቅር ፍቅር አይደለም" ፍቅር ዘላለማዊ ሰላም እንደሆነ ይነግራቸዋል ። እኛ ከተራራው ግርጌ ያለን ሰዎች ስለ ፍቅር ያለን ምልከታ የተለያየ ነው ። ሚርዳድ ግን "ፍቅር በሕይዎት ዜማ ላይ የሚደንስ ሰላም ነው " ይለናል ። ፍጹም እና ዘላለማዊ ሰላም ከተራራው ጫፍ ከአለው ገዳም አበምኔት ይነገራል ይኖራል። ~~~~~~~~ √√ መጽሐፈ ሚርዳድ " ሙሉ መጽሐፉ ጥቅስ በሚመስሉ ሐረጎች፣ ዓረፍተ ነገሮች እና ግጥሞች የተሞላ ድንቅ መጽሐፍ ነው ። ለምሳሌ ለአብነት ያህል እንዲህ ይላል " ****** ❝ ሰዎች ግን ብርሃኑን ካላያችሁ ብላችሁ አትጣሩ ብርሃን የሚፈልጉ ጋባዥ አይፈልጉም ❞ ****** ❝ሁሉን ስታውቁ ፣ ያኔ፣በማንም ላይ አትፈርዱም❞ ****** ❝በፀሐይ ፊት መንደድን የሚያፍር ሻማ ሀጢአት አለበት❞ ***** ❝በልቡ ውስጥ ቤተ መቅደስ ማግኘት ያልሆነለት ፣ በየትኛውም ቤተ መቅደስ ውስጥ ልቡን ሊያገኝ አይሆንለትም ❞ ******** ❝ለለውጥ የሞተ ለለውጥ አልባነት ይወለዳል❞ ******* ❝ግልድማችሁን ካላወለቃችሁ ከእግዜር አትደበቁም ❞ ***** ❝እግዚአብሔርን ለሚሻ ልብ ሁሉም መንገዶች ወደ እግዚአብሔር ይወስዳሉ❞ ***** ❝መንገዳችሁን ቀጥሉ። በእያንዳንዱ መታጠፊያ አዲስ ጓደኛ ታገኛላችሁ❞ ***** ¶¶ አጋዘን አዳኙ እና ባለቅኔው ¶¶ በዚህ ዓለም ላይ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች አሉ። አንዱ አጋዘን አዳኝ ነው ሌላኛው ባለቅኔ ነው ።አጋዘን አዳኙ " አጋዘኗን አይቶ ገድሎ ለመብላት ሲቋምጥ ፤ ባለቅኔው ግን ያችኑ አጋዘን ሲያይ በአንዳች አክናፋት ተጭኖ አዳኙ አልሞት ወደ ማያውቀው ቦታ እና ጊዜ ይሸመጥጣል" ይላል ። አጋዘን አዳኙ ቀስቱን ወድሮ ግዳይ ሊጥል ጫካውን እያካለለ ሲሮጥ አጋዘን ገድሎ በጀብድ እየፎከረ የአጋዘን ሥጋ እየተመገበ ሃሴት ሲያደርግ ፤ ባለ ቅኔው ደግሞ ያችን ውብ አጋዘን ከንጹህ ወራጅ ፏፏቴ ማዶ ከደኑ ሥር ሲመለከታት መንፈሱ ሥጋውን ከድታው በውበት ባሕር ይሰምጣል፣ ፈጣሪ ሆኖ ሁነቱን እንዳለ ሊያዜመው ይዳዳዋል ... ታዲያ በማያቋርጥ ሰላም ሕይዎትን በሃሴት የኖረው አዳኙ ነው ? ወይስ ባለቅኔው? ብለን እንድንጠይቅ ይጎተጉተናል። ~~~~~ ¶¶እንደ ማጠቃለያ¶¶ መጽሐፈ ሚርዳድ የሰው ልጅ ወደ ውስጡ በመመልከት፣ አዲስ ዓለም በመፍጠር ፣ ምንታዊነትን አጥፍቶ ፍፁም ፍቅር ፣ሰላማዊ ፣ እውነተኛ ፣ ውህደት ያለው ዘላለማዊ ሕይዎት መኖር እንደሚችል የሚናገር በአይነቱ ልዩ የሆነ ጥልቅ መንፈሳዊ መጽሐፍ ነው ። መጽሐፉ ከምናየው ዓለም ያፈነገጠ ፣ ለመረዳት ከባድ የሆነ ፣ በነገረ እውቀት መንገድ በቀላሉ ለመተንተን የሚያስቸግር ሆኖ ሳለ በስነ ጽሑፍ ውበቱ እና በሚያነሳቸው ሚስቲክ ሃሳቦች ደግሞ እጅጉን መሳጭ የሆነ ድንቅ መንፈሳዊ መጽሐፍ ነው ። ዋናውን የእንግሊዘኛውን መጽሐፍ ያነበቡ ትርጉሙ ላይ አስተያየት ቢሰጡበት ጥሩ ነው ። በጸጋው ማሞ
Comments (0)
Login to leave a comment.
T
Tsegaw Mamo
2 reviews · 0 followers
View All Reviews
Have you read this book?

Share your own review and help the community.

Write a Review
Get it on Google Play