ርዕስ : ሀገር ምንድር ናት ?
ደራሲ : " ዓለማየሁ ሞገስ "
ዘውግ : ፍልስፍና
የሕትመት ዓመት : 1953 ዓ.ም
ሀገር ምንድር ናት? የገፅ ብዛቷ 33 ሲሆን በገንዘብ እጦት ታይፕ እየተደረገች የተሰራጨች ናት። ስለ ሀገር፣ የሃገር ጠላት፣ ሕዝብ ፣ ሰንደቅ ዓላማ ፣ ነጻነት ፣ ኅብረት ፣ ባህል ፣ መሪ ፣ ምክር ቤት ፣ ዘውድ ፣ የሀገር ፍቅር ጉዳዮች መግቢያ እየጻፉ በግጥም የገለጹበት ግሩም መጽሐፍ ሆና አገኘኋት ። እጅግ ወደድኳት።
በመጀመሪያ "መልክዐ ኢትዮጵያ " በማለት በቅኔያዊ መንገድ የጻፉት ቢሆንም ለተርታው ሰው ግልጽ ባለመሆኑ እንደገና "ሀገር ምንድር ናት " በሚል ርእስ ለህጻናት ጭምር በሚገባ መንገድ እንደጻፉት በመግቢያው ላይ ተናግረዋል ።
"ደስ እንዲልህ ከፈለግህ ተፈጥሮን እንዳለች ተቀበል ፣ መጥፎን ልማድ አሻሽል ፣ የማይመረምርን ሰው ልማድ ይገዛዋል " እያሉ ገና በጠዋቱ በማይጠቅሙን ልማዶቻችን ላይ አብዮት ለማስነሳት የተንቀሳቀሱት ታላቁ ባለቅኔን መምህር ዓለማየሁ ሞገስን እንዘክራቸው ዘንድ ይገባል ። በእርግጥ አንድ "አብረሃም" የሚባል ጓደኛዬ የእርሳቸውን መጽሐፍ ሁሉ እንደሰበሰበ ሰሞኑን በአድናቆት እያጫወተኝ ነበር ። ትላንት ማታ ላይ አራት ኪሎ በመንገድ ላይ ኤርፎን አድርጌ እየተጓዝኩ ሳለ አንድ እጅ ድንገት ያዘኝ...ዞር ስል በፍጹም አክብሮት ከምወዳቸው የመጽሐፍ አዟሪ አንዱ ነበር ። መንገድ ላይ እንዳንሸጥ ተከልክለናል " አርሙኝ በእርግጥ አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም እና ሌሎችም " የሚለው የራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው መጽሐፍ አለኝ ግዛኝ አለኝ ።
በእጅጉ እየተደሰትኩ እሺ ብየው የጋራ መጽሐፍ መደብራቸው ስሄድ እጅግ የማከብራቸውን "የማሞ ውድነህን" የማላውቃቸውን መጽሐፍት የነ ሸክስፒር መጽሐፍትን በሚያስደንቅ ሁኔታ አገኘኋቸው ። ቀጥዬ የዓለማየሁ ሞገስ መጽሐፍ አለህ ? አልኩት ...ፈገግ አለና ...አዎ አለኝ ። "ሀገር ምንድር ናት " የምትለውን መጽሐፍ መዥረጥ አድርጎ ሰጠኝ እና ይኸን ያህል ክፈል አለኝ ። ምን አማራጭ አለኝ... በፍቅር ነው የሸመትኳት ።የሚያስደንቁኝን የታላላቆችን የአእምሮ ጭማቂ ገዝቶ እንደማንበብ ያለ ሃሴት ምን አለ?
ለምሳሌ የሀገር ፍቅር ከሚለው ርእስ ስር እንዲህ ይላሉ"ከሃይማኖት በልጦ ዓለምን የሚገዛ እንደ ሀገር ፍቅር ያለ ትልቅ ፍልስፍና የለም" እያሉ በግጥም ያብራራሉ ። መሪ በሚለው ርእስ ስር ደግሞ " ያንድ ሀገር ሥልጣኔና ዕድገት ብዙ ጊዜ እንደመሪው ይሆናል። በትጉሁ ጊዜ ይዳብራል፣ በሰነፋ ጊዜ ይኮስሳል ፣ በጥቅም አባራሪ ጊዜ ይወድማል ፣ ባጭበርባሪ ጊዜ ይጠፋል " ይላሉ ። " ዓለማየሁ ሞገስ " በዚያን ጊዜ እጅግ ተራማጅ ትጉህ የነበሩ ከ20 መጽሐፍት በላይ የጻፉ ሊቅ ናቸው። በተለይ "ልማድ እና ሠርግ " ግሩም መጽሐፋቸው ነች ። ዘመናቸውን ሲያነቡ ፣ ሲጽፉ እና ሲያስቡ የኖሩ ሊቅ ናቸው ።
[Reviewer : Tsegaw Mamo is an associate editor at Think Ethiopia Book Review]
Please login to view seller contact details.