የሕክምና ገዳም

Negotiable

Price is negotiable
Condition: New
Category: Biographies & Memoirs
Language: Amharic
Location: Addis Ababa (4 Kilo)
Description

“የሕክምና ገዳም”
----------------
የዶ/ር በድሪ ሙኒርን መጽሐፍ አንብቤ ስጨርስ በእውነት ተደሰትኩ፡፡ በዚህች መጽሐፍ ታትሞ መውጣት የብዙ ሰው ዐይን እንደሚገለጥ እርግጠኛ ነኝ፡፡

በድሪ ለአስርት ዓመታት ከተጓዘበት የሕይወት መንገድ በአዕምሮው ከመዘገበው ውስጥ የአዳማና ጎንደር ቆይታውን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ አካትቶ ተርኮልናል፡፡ ነፍስ ካወቀበት ጊዜ አንስቶ የሚያስታውሳቸውን ጉልህ ክስተቶች በሚያስጎመጅ መንገድ አቅርቦልናል፡፡ ዛሬን እየኖረ 'ትናንት እንዴት ነበር' ብሎ ለሚጠይቅ ሰው ጠቃሚ መረጃ የተካተተበት ሥራ ሆኖ ታይቶኛል፡፡ እጅግ የሚደነቅ አበርክቶ ነው፡፡

እሱ ጎንደር የገባው ከእኔ አንድ ዓመት በኋላ ስለነበር በኮሌጁ ዙሪያ የጠቀሳቸውን ነገሮች በአብዛኛው እኔም አስታውሳቸዋለሁ፡፡ ወደ ጥቃቅን ዝርዝሮች ስንገባ ግን ትውስታችን በአንዳንድ ነጥቦች ላይ የተራራቀ መስሎኛል፡፡ የተወሰኑ ኩነቶችን እሱ በገለጸበት ደረጃ እኔ በዝርዝር አለማስታወሴ ድሮ በሳይኮሎጂ ትምህርት ስለ Memory የተማርነውን መከለስ እንዳለብኝ አስታወሰኝ፡፡ በዚያው መጠን እሱ የዘነጋቸውን ነገሮችም አግኝቻለሁና ጥቂት ክለሳ ማድረጌ አይቀርም፡፡

የመተከል ዘመቻን በተረከበት ምዕራፍ እጅግ ተደንቄያለሁ፡፡ እዚያ እያለሁ ልብ ባላልኩት ሁኔታ የዘማቹ ኑሮ የተለያየ እንደነበር ከ40 ዓመት በኋላ ነው የተገነዘብኩት! ይህን የምለው ሁለታችንም በአንድ ጣቢያ (አይሲካ/አይሲድ) የነበርን መሆኑን መሠረት አድርጌ ነው፡፡ የእኔና የቅርብ ጓደኞቼ ትዝታ በአብዛኛው በመዋኛ ቦታችን ዙሪያ በነበሩ ትርዒቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን እሱና ጓደኞቹ ደግሞ ከዚያም የሰፋ ጀብዱ ሲፈጽሙ እንደነበር ያወቅኩት አሁን ነው፡፡

መተከልን አስመልክቶ በፌስቡክ ተከታታይ ጽሑፎች ሳወጣ እንደጠቀስኩት የሰነቅኩት ተስፋ በዘመኑ በዘመቻው የተሳተፉ ወገኖች (ጋምቤላን ጨምሮ) ትውስታቸውን ቢያካፍሉን የልጆቻችን ትውልዶች ስለዚያ ዘመን ጠቃሚ መረጃ ሊያገኙ ይችላሉ የሚል ነበር፡፡ የበድሪ መጽሐፍ በዚህ በኩል ጉልህ አስተዋጽዖ ተደርጎ መቆጠር አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡

ከመተከል ወደየተቋማችን ስንመለስ ስለተገለበጠው አውቶቡስ ጉዳይ በድሪ የጠቀሰው የሟቾች ቁጥር አጠራጣሪ ሆኖ ተሰምቶኛል፡፡ እኔ እንደማስታውሰው የሞቱት ልጆች ቁጥር 6 የነበረ ሲሆን ከእነሱም መካከል ሁለቱ በአውቶቡሱ ውስጥ መገኘት ያልነበረባቸው እንደነበሩ በጊዜው ሲነገር ሰምቻለሁ፡፡ አውቶቡሱ ሦስት ጊዜ ተንከባልሎ ሲቆም ሁሉም ተሳፋሪዎች አለማለቃቸው ሁላችንንም ያስደነቀ ጉዳይ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ (በዚህ ጉዳይ ላይ ራሱን የቻለ ጽሑፍ ማውጣቴ ትዝ ይለኛል፡፡) የሟቾቹን ቁጥር በተመለከተ አሁንም በሕይወት ያሉትን አስተባባሪዎች /ለምሳሌ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላን/ ለመጠየቅ እሞክራለሁ፡፡

መጽሐፉ ሁለተኛ እትም የሚኖረው ከሆነ መስተካከል ያለባቸው አንዳንድ ስሞች፣ ቀኖችና ግጥሞች አሉ፡፡ እነዚህን ለበድሪ በግሉ እነግረዋለሁ፡፡

ይህ መጽሐፍ ከያዘው እጅግ ጠቃሚ መረጃ በተጨማሪ ከሽያጩ የሚገኘው ገቢ በሙሉ የሴቶች ማረፊያና ልማት ማሕበር ለሚባለው የበጎ አድራጎት ድርጅት የሚሰጥ በመሆኑ የቻላችሁ ሁሉ ገዝታችሁ እንድታነቡት አደራ እላለሁ፡፡

በድሪ፡ በድጋሚ እንኳን ደስ አለህ!

© ዶ/ር እንዳለማው አበራ

Marketplace

Seller Information

Please login to view seller contact details.

Please login to view seller contact details.
Share
Please login to express interest in this book.
Get it on Google Play