ኃይለመለኮት መዋዕል ማናቸው ?

ኃይለመለኮት መዋዕል መሐሪ ሰኔ 16 ቀን 1943 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ፣ ይፋትና ጥሙጋ አውራጃ ማጀቴ ከተማ ተወለደ። የልጅነት ጊዜውን በኮምቦልቻ፣ በአስመራ እንዲሁም በአዲስ አበባ ያሳለፈ ሲሆን፣ በጊዜው አማርኛና ትግርኛ ቋንቋዎችን ጠንቅቆ ለማወቅ ችሏል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በኮምቦልቻና በአስመራ (ከ5ኛ-8ኛ ክፍል) ከተማረ በኋላ ሁለተኛ ደረጃን በልዑል መኮንን ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ትምህርት ቤት አጠናቋል።

ከ1962 ዓ.ም. ጀምሮ በዓለም ማያና በሕዝብ ትምህርት ቤቶች በመምህርነት ማገልገል የጀመረው ኃይለመለኮት፣ ለ33 ዓመታት በሙያው ሲያገለግል ቆይቶ በ2003 ዓ.ም. በጡረታ ተገልሏል። በሥራ ዘመኑ የመምህራንን መብት ለማስከበር በተደረጉ ትግሎች ንቁ ተሳታፊ የነበረ ሲሆን፣ የግል ትምህርት ቤቶች መምህራንና ሠራተኞች ማኅበር ፕሬዚደንት ሆኖም አገልግሏል። በ1966 ዓ.ም. በሥራ ማቆም አድማ ወቅት እንዲሁም ከ1969 እስከ 1971 ዓ.ም. በደርግ ዘመን በፖለቲካ ምክንያት ለእስራት ተዳርጎ ነበር።

ኃይለመለኮት በሥነ-ጽሑፍ ዘርፍም ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከተ ደራሲ ነው። «የወዲያነሽ» እና «ጉንጉን» የተሰኙት ዝነኛ ልብ ወለዶቹ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ማስተማሪያ ለመሆን በቅተዋል። ከዚህም በተጨማሪ እንደ «ፀላም መቐነት»፣ «ጋህሲ ስቓይ» እና «መገሻ ዓሻ» ያሉ የትግርኛ ተውኔቶችን የጻፈ ሲሆን፣ የዊልያም ሼክስፒርን «ኦቴሎ» ተውኔት ወደ ትግርኛ ተርጉሞ በ2006 ዓ.ም. አሳትሟል። ከ750 በላይ እንካስላንቲያዎችን የያዘ መጽሐፍ ያዘጋጀው ደራሲው፣ በትምህርት ሚኒስቴር የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር መጻሕፍት ዝግጅት ላይ ከመሳተፉም ባሻገር ከ80 በላይ የሚሆኑ የሌሎች ደራስያንን መጻሕፍት በአርታኢነት አቅንቷል።