ሕይወት ተፈራ ማነች?
ሕይወት ተፈራ ያደገችው በሀረር ከተማ ሲሆን፣ የልጅነት ጊዜዋን ከተለያዩ ጨዋታዎች ጋር ባማረ ሁኔታ አሳልፋለች። ለንባብ የነበራትን ፍቅር ያዳበረችው በወላጆቿ አባቷ ተፈራ ምንዳ እና እናቷ ጠንፍየለሽ ደምሴ የንባብ ባህልና አበታችነት ነበር። ገና በ3ኛ ክፍል ተማሪነቷ የመኮንን እንዳልካቸውን “ፀሐይ መስፍን” መጽሐፍ ያነበበች ሲሆን፣ በሀረር መድኃኔዓለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በነበረችበት ወቅትም አባቷ የሚመርጡላትን እንግሊዝኛ መጽሐፍት ታነብ ነበር።
በ1965 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (የአሁኑ አዲስ አበባ) ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀለች ሲሆን፣ በወቅቱ በነበረው የነቃ የተማሪዎች ንቅናቄ ምክንያት በሁለተኛው መንፈቅ ዓመት የፖለቲካ ጥናት ክበብ በመቀላቀል የኢህአፓ አባል ሆናለች። በዚህም ንባቧ ወደ ማርክሲስታዊ አስተሳሰብ ያደገ ሲሆን፣ በ1966 ዓ.ም አብዮቱ ሲፈነዳ ትምህርቷ ተቋረጠ።
ትምህርት ከመቋረጡ በፊት ህይወትና ጓደኞቿ የሚያደርጉትን የሶሻሊዝም ጥናት ይመራ የነበረውን ደንገርገር ያለ ዓይን አፋር ወጣት — ጌታቸው ማሩን ተዋወቀች። የህብረተሰብ ሳይንስና የፖለቲካ ጥናት በሚያደርጉበት ወቅት እግረ መንገዳቸውን በፍቅር ወደቁ። ሆኖም ግን ፍቅራቸው ከቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ከያዟቸው የፖለቲካ ፓርቲ ጭምር የተሰወረ ምስጢራዊ ነበር።
በ1969 ዓ.ም የፓርቲ አባላት ልዩነት ውስጥ በገቡበት ወቅት፣ የሃሳብ ልዩነት በውይይት ይፈታ ይል የነበረው የትግሉ መሪ ጌታቸው ማሩ በገዛ ጓዶቹ ተገደለ። የጌታቸው ሞት በህይወት ላይ ከፍተኛ የስነ-ልቦና ስብራትና መንገብገብ አሳደረባት። ከግድያው በኋላ ህይወት ሞትን እየሸሸች ለአንድ ዓመት ያህል በፍርሃትና በድብብቆሽ ካሳለፈች በኋላ፣ በ1970 ዓ.ም በካቲት ወር በቁጥጥር ስር ውላ የ15 ዓመታት እስራት ተፈረደባት። በእስር ቤት ቆይታዋ ቀንሳው የነበረውን የንባብ ልምዷን ያበረታች ሲሆን፣ ስለ ጌታቸውም ለመጻፍ ሞክራ ነበር፤ ነገር ግን እስር ቤቱ ሲፈተሽ የጻፈችውን አውጥታ ለመጣል ተገዳለች። በከርቼሌ እስር ቤት ውስጥ 8 ዓመት ከ4 ወር ካሰረች በኋላ ሰኔ 1978 ዓ.ም በምህረት ተፈታች።
ከተፈታች በኋላ በ1979 ዓ.ም መስከረም ላይ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብትመለስም፣ ከተወሰኑ ወራት በኋላ በተነሳው ተማሪዎች አድማ ምክንያት ቤተሰቦቿ ስለ ደህንነቷ ሰግተው ወደ ጣልያን ሀገር ላኳት። በጣልያን ሁለት ዓመት ከቆየች በኋላ ወደ ካናዳ ተሸጋገረች። በካናዳ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ በ"People to People Canada" ድርጅት ውስጥ በኮኦርዲኔተርነት፣ በ"Center for Women" ውስጥ ለ2 ዓመታት ከምርምር ጋር በተያያዙ ሥራዎች እንዲሁም በካናዳ መንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ በጥሩ ክፍያ አገልግላለች።
ከ20 ዓመታት በላይ በስደት ከቆየች በኋላ፣ በትምህርት ቤት ቆይታዋ ከመጻፍ ጋር በተያያዙ ኮርሶች ያመጣችው ከፍተኛ ውጤት፣ የመምህሮቿ አበታችነት እና የልጅነት የንባብ ፍቅሯ ተዳምረው ስለ አብዮቱ፣ ስላሳለፈችው የእስር ቤት ህይወትና ስለ ጌታቸው ማሩ ታሪክ የሚተርከውን “Tower in the Sky” የተሰኘውን የመጀመሪያ መጽሐፏን በእንግሊዝኛ ጽፋ አሳተመች (መጽሐፉ በኋላ በጌታነህ አንተነህ ወደ አማርኛ “ማማ በሰማይ” በሚል ተተርጉሟል)።
ከ26 ዓመታት የስደት ህይወት በኋላ ወደ ሀገሯ በዘላቂነት በመመለስ “Mine to Win” የተሰኘውን ሁለተኛ ልቦለዷን እና “ምንትዋብ” የተሰኘውን ታሪካዊ ልቦለድ አሳትማለች፤ መጽሐፉም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይቀሩ በፌስቡክ ገጻቸው ያመሰገኑበት ስራ ሆኗል። ወደ ሀገር ቤት ከተመለሰች በኋላ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና በኢትዮጵያ ሴቶች ጤና ማህበር ውስጥ የሰራች ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የሙሉ ጊዜ ደራሲ ለመሆን እየሰራች ይገኛል፤ አራተኛ መጽሐፏንም ለአንባቢያን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ትገኛለች።

Comments (0)
No comments yet. Be the first to comment!